ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ የሚያገናኙ የዘመናዊ ባቡር መስመሮች ባለቤት ለማድረግ መትጋት አለብን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ የሚያገናኙ የዘመናዊ፣ ፈጣንና ጥራት ያለው የባቡር መስመሮች ባለቤት ለማድረግ መትጋት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መስመር የአሸናፊነታችን ውጤት ነውም ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ይህን ያሉት የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የአንድ ዓመት አፈጻጸም እና የሠራተኞች ቀንን በተመለከተ በተዘጋጀው መርኃ ግብር ላይ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባቡር መሠረተ ልማት እውን በማድረግ በአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተጠቃሽ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከጂቡቲ-ሐረር፣ ከሐረር ተነሥቶ አዲስ አበባ እንጦጦ እና ከእንጦጦ ወደ ጂማ በማምራት እስከ ነጭ ዓባይ ድረስ የሚዘረጋ የባቡር መስመር ፕሮጀክት በሦስት ምዕራፍ ለመገንባት አቅዳ እንደነበር አውስተዋል።

ይሁንና ማሳካት የተቻለው ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጀመርነውን ያለማስቀጠል ችግር በመኖሩ የባቡር መሠረተ ልማቱ ከውስጥም ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትም ሳይስፋፋ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን አስሮ የያዛትን ጀምሮ ያለመጨረስ ስብራት ለመጠገን ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ “ከጀመርን ሳንጨርስ አናርፍም” ብለን ተነስተናል ነው ያሉት።


 

በ'ዋን ቤልት ዋን ሮድ ኢንሼቲቭ' መሠረት በኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መሠረተ ልማትን እ.ኤ.አ በ2018 እንደገና አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ የታሰበውን ያህል አለማሳካቱን እና የሠራተኞችን ደመወዝ መክፈል ተስኖት የመንግሥት ዕዳ ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

በዚህ የተነሳም መንግሥት የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሪፎርም ማድረጉን፣ በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ማዘመኑን ጠቅሰዋል።


 

በተለይ የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ሙያተኞች በጋራ ማስተዳደር ከጀመሩበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማየት ጀምረናል ነው ያሉት።

በርካታ መንገደኞችን እያጓጓዘ እንዲሁም የገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን በማሣለጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመግለፅ፤ በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት የግንኙነት አድማስን እንዲያሰፋ በትጋት መስራት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ለዚህም የባቡር መሠረተ ልማቱን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ፈጣንና ጥራት ያለው ማድረግ፣ የተጀመሩ የባቡር መሥመር ግንባታዎችን ችግር በጥናት በመፍታት ሥራውን መጀመር ይጠበቃል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያን የዘመናዊ ባቡሮች ሀገር ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም፥ ሌሎች አዳዲስ የባቡር መሥመሮችን በመገንባት የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር የአንድ ለእናቱ ስያሜ ታሪክ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም