የአረንጓዴ አሻራ የብልፅግና ጉዞን እያሳካ አለምአቀፋዊ ትስስርና መልካም ወዳጅነትን እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ የብልፅግና ጉዞን እያሳካ አለምአቀፋዊ ትስስርና መልካም ወዳጅነትን እያጠናከረ ነው
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 26/2017(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ የብልፅግና ጉዞን እያሳካ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ትስስርና መልካም ወዳጅነትን እያጠናከረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ተናገሩ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎትና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮች ቡድን አባላት በድሬዳዋ ዛሬ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ክንውኑም " በመትከል ማንሰራራት " በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን፤ በተጨማሪም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለተማሪዎች የትምህርት ቁሶች ድጋፍ በማድረግ አስጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ የአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የብልፅግና ጉዞ እያሳካ የሚገኝ ሀገራዊ መርሃ ግብር ነው ።
የአረንጓዴ አሻራ በአለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀስ ድንቅ ስራ እየሆነ ይገኛል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ በጎረቤት እና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት የችግኝ ተከላ በማካሄድ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር መቻሉን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ከሀገራዊ ፋይዳው ባለፈም ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ በረከቶችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የዲፕሎማሲያችን ማረጋገጫ ሆኗል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ከሀገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነትና ወንድማማችነትን ለማፅናትና የአብሮነትና የትብብር ስሜት እንዲጎለብት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልጸዋል።
መትከልና ማሳደግን ባህል በማድረግ የደን ሽፋናችንን መጨመርና ያሉትን መጠበቅ ይገባናል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመንን ከግብ እያደረሰ የሚገኝ መርሃ ግብር መሆኑን ተናግረዋል።
በድሬዳዋ ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች ድሬዳዋን ውብና አረንጓዴ ከተማ እያደረጋት ይገኛል ብለዋል።
የተተከሉት ችግኞች ደርሰው ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ከመከላከል ባለፈ የግብርና ምርትና ምርታማነት ጎልብቶ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዙ መሆኑን አንስተዋል ።
በተጨማሪ በድሬዳዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት እና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።