የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ እና የወል ትርክት መገንቢያ ነው- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ እና የወል ትርክት መገንቢያ ነው- የምክር ቤት አባላት
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ)፡ - ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ እና የወል ትርክት መገንቢያ መሆኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመንግስት ብስለት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ጥረት፣ የመፈፀም አቅምና የህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ታክሎበት እውን የሆነ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ማሳያ እና የወል ትርክት መገንቢያ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል እናትነሽ በዛብህ (ዶ/ር) ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ የኢትዮጵያውያን እልህ አስጨራሽ የልማት ጥረት እና የመንግስት የመፈፀም አቅም የታየበት እንዲሁም በአብሮነት የትኛውንም ልማት መከወን እንደሚቻል የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ መገንባት ከኢትዮጵያም ባለፈ የአካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭ በመሆኑ የአፍሪካዊያን ኩራት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሌሎች የልማት ስራዎችን በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ፋጡማ ይማም፤ የህዳሴ ግድብ ከሃይል ምንጭነትም ባለፈ የቱሪዝም ሃብት፣ የዓሣ ልማትና የአካባቢ ስነ ምህዳር መጠበቂያ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በግንባታው ሂደት በውስጥና ከውጭ በርካታ ፈተናዎች የገጠሙ ቢሆንም የታለፈባቸው መንገድ ብዙ ትምህርት የተወሰደበት መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ አብዱ ይማም፤ የሕዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ የማይደበዝዝ አሻራ፣ የልማት አርበኝነት መገለጫና የኩራታችን ምንጭ ነው ብለዋል።
ኢትዮጰያውያን በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው የተሳተፉበት፤ በርካቶች መስዋእትነት ጭምር የከፈሉበት መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ግድቡ የጋራ የሀገር ሃብት፣ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ማሳያና የጥንካሬ መገለጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል።