ቀጥታ፡

ዋልያዎቹ የወዳጅነት ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ) :- ወደ አሜሪካ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6 ሰዓት ላይ በዋሺንግተን ዲሲ ኦውዲ ፊልድ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድን ለወዳጅነት ጨዋታው ከሐምሌ 16 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዝግጅቱን አድርጓል።


 

ቡድኑ ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ አሜሪካ በማቅናት ዝግጅቱን የቀጠለ ሲሆን ትናንት የመጨረሻ ልምምዱን ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

ለአሜሪካው ሎውደን ዩናይትድ የሚጫወተው ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆኗል። ሌሎቹ የቡድን አባላት በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ዋልያዎቹ ወደ አሜሪካ በማቅናታቸው 25 ሺህ ዶላር እንደሚያገኝና ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ ተጨማሪ 50 ሺህ ዶላር እንደሚበረከትለት ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።  

የወዳጅነት ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ ለሚያደርጋቸው የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች መዘጋጃ እንደሚሆነውም ተነግሯል።

ዲሲ ዩናይትድ እ.አ.አ በ1994 የተመሰረተ ክለብ ሲሆን ተቀማጭነቱ በዋሺንግተን ዲሲ ነው። በጊዜያዊው አሰልጣኝ ከዌቨን ፍላናጋን የሚመራው ቡድን በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር እየተወዳደረ ይገኛል።

ቤልጂየማዊው የቀድሞ የሊቨርፑል፣ አስቶንቪላ እና ክሪስታል ፓላስ አጥቂ ክርስቲያን ቤንቴኬ፣ ብራዚላዊው ጆአኦ ፔግሎው እና ኮስታሪካዊው ራንዳል ሊል ከቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።   

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ አምርቶ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ የሚያስችለውን የሶስት ዓመት ስምምነት ከዲሲ ዩናይትድ ጋር መፈራረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም