ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ - የሀገራዊ ህዳሴ ምልክት፤ የብልጽግና ፍኖት ማሳያ

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ህዝብን ለጋራ ዓላማ ያሰባሰበ፣ የአገርን ገጽታ ለመቀየር የታለመ እና ለትውልድ የሚሻገር ራዕይ የሰነቀ ፕሮጀክት ነው። በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን፣ የተራቆተውን የሀገር መልክዓ ምድር በማደስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና ዘላቂ ብልጽግናን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያለመ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ ግብ ችግኝ መትከልና የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ግንባታ፣ የህዝብ አንድነት እና የኢኮኖሚ ልማት ማዕከል ማድረግ ነበር። ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑና ለጋራ ብልጽግና በጋራ እንዲሰሩ እድል የፈጠረ ህዝባዊ ንቅናቄ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ ስኬት የሚለካው በተተከሉት ችግኞች ብዛት ብቻ አይደለም። መርኃ ግብሩ የተነደፈው ዘርፈ ብዙ እና እርስ በርስ የተሳሰሩ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ነው። ከነዚህ መካከል የተወሰኑትን መዝዘን እንመልከት።

  1. የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም

ይህ የንቅናቄው ዋነኛ ግብ ነው። የተራቆቱ ተራሮችን እና መሬቶችን በደን በመሸፈን የአፈር መሸርሸርን መከላከል፣ የበረሃማነት ስርጭትን መግታት፣ የካርበን ልቀትን መቀነስ እና ሀገሪቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በቀላሉ እንድትላመድ ማስቻል ቁልፍ ዓላማዎች ናቸው። በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት በምርትና ምርታማነት ማደግ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል።

  1. የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ልማት

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ከጥላ እና የደን ዛፎች ባለፈ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን እንዲሁም እንደ ቡና እና ሻይ ያሉ የገቢ ምንጭ የሆኑ ችግኞችን በስፋት መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ገቢ ለማሳደግ ያለመ ነው። በተጨማሪም፣ ለእንጨት ኢንዱስትሪ፣ ለማር ምርት እና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ተክሎችን በማልማት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ይደግፋል። ለዚህም ነው ውበትም ህይወትም ነው የሚባለው።

  1. ሀገራዊ አንድነት እና የህዝብ ተሳትፎ

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከገበሬው እስከ ከተሜው፣ ከተማሪ እስከ መንግሥት ሰራተኛ፣ ከሃይማኖት መሪዎች እስከ የጸጥታ አካላት ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዓላማ ስር አስተባብሯል፤ አስተሳስሯል። ይህ የጋራ ግብ ተሰንቆ እየተተገ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የወል ትርክት መሠረት ጭምር እየሆነ ይገኛል።

  1. አረንጓዴ ዲፕሎማሲ

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ድንበር ተሻግሮ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጭምር ምሳሌ ሆኗል። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በመለገስ የአካባቢ ጥበቃ የጋራ አጀንዳ መሆኑን በተግባር አሳይታለች። ይህም "አረንጓዴ ዲፕሎማሲ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በሀገራት መካከል በጎ ግንኙነትን ለማዳበር አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እየሰራም ይገኛል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ፣ ዛፎችን የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የተስፋ፣ የህብረት እና የሀገራዊ ህዳሴ ምልክት ነው። የዛሬዎቹ ችግኞች የነገዎቹ ደኖች፣ የነገዎቹ የውሃ ምንጮች እና የነገው ትውልድ ንጹህ አየር ናቸው። ይህ ንቅናቄ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳየችበት፣ ዜጎቿም ለሀገራቸው እድገት በጋራ ሲቆሙ ምን ያህል ታላቅ ነገር መስራት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ዛሬ የተተከለው እያንዳንዱ ችግኝ ለነገዋ አረንጓዴ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚቀመጥ ጠንካራ የማዕዘን ድንጋይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም