ቀጥታ፡

ለአዲሱ ትውልድ የሳይበር ደህንነት እውቀትና ክህሎት ማስታጠቅ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ ለአዲሱ ትውልድ የሳይበር ደህንነት እውቀትና ክህሎት የማስታጠቅ ተግባር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ገለጹ፡፡

የ2017 ዓ.ም የክረምት የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሒዷል፡፡


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ከማል ኢብራሄምን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡    

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ለአዲሱ ትውልድ የሳይበር ደህንነት እውቀትና ክህሎት ማስታጠቅ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡

የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን አስታውሰው፤ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለተወጣጡ ታዳጊዎች የሳይበር ታለንት ስልጠናዎችን በሶስት ዙሮች ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወጣቶቹ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው ለአገር የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ክረምት ለአራተኛ ጊዜ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለተወጣጡ 784 ታዳጊዎች ስልጠና መስጠት መጀመሩን አመላክተዋል፡፡

ከነዚህ ሰልጣኞች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሳይበር ልማት ማዕከል እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰለጥኑ ገልጸዋል።

የዲጅታል ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል በራስ አቅም ለሳይበር ሰራዊት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ከማል ኢብራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለክረምት የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ተከታታዮችን ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በዬነ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሰልጣኞች በክረምቱ ወቅት የዲሲፕሊን፣ የስነ ልቦና እና በመረጧቸው የትምህርት ዘርፎች የቴክኒክ ስልጠና ይሰጣቸዋል።  


 

ከአዲስ አበባ ከተማ ሰልጣኝ ሒስኑል መሐመድ በዘርፉ አገሯን ለማገልገል የተሰጠውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን  አስታውቃለች፡፡ 


 

ከኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሰልጣኝ ያኔት ተስፋዬ፤ በፕሮግራሙ ያገኘው እድል ያለውን አቅም በማውጣት ህልሙን ለመኖር እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል፡፡

የስልጠና ፕሮግራሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ አገራችን ለማገልገል የሚያስችለን እውቀት የሚያስይዘን ነው ያለው ደግሞ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጣው ያሬድ ብርሃኑ ነው ፡፡ 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ከክረምት የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በኋላ ከሰልጣኞች ጋር በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም