ቀጥታ፡

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የህክምና አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄዷል።


 

በማስጀመሪያው ላይ በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢሉባቡር ቦኖ እንዳሉት፤ የጤና ህክምና በበጎነት የሚተገበርና ለሌሎች የመኖር ተግባር ነው።

በአገልግሎቱ የሚሳተፉ የህክምና ባለሙያዎች አቅም ለሌላቸውና ከቤት መውጣት ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ህክምና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተጠባባቂ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንዱዓለም ደነቀ እንደገለጹት ፤ የበጎ ፍቃድ ተግባር ከማህበራዊ ጥቅሙ ባሻገር የሚሰጠው የስነ ልቦና እርካታ ከፍተኛ ነው።

ይህን መልካም ተግባር እንደ ሀገር ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበው የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባራትን መነሻ በማድረግ ቋሚ አገልግሎቶችን ማደራጀትና ማስቀጠል እንደሚቻልም ገልጸዋል ።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዱራዛቅ መሀመድ፤ ሆስፒታሉ የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በክረምት በጎ ፍቃድ የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤና ለማሻሻል የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

የሆስፒታሉ የድንገተኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ትዕግስት ወርቁ በበኩላቸው፤ በጎ ፍቃድ የሙያቸው አንዱ አካል በመሆኑ እየሰሩበት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የህክምና ሙያ ቅንነትና ለሰዎች መሰጠትን የሚጠይቅ በመሆኑ በየቀኑ የሚሰሯቸው ስራዎች የበጎነት ተምሳሌት በመሆናቸው ይህንኑ አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የህክምና ሙያ ከመደበኛ ስራ በተጨማሪ በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አስማረ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም