በሲዳማ ክልል ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሀዋሳ፤ ሃምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሲዳማ ክልል የተከናወኑ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2017 ክልል አቀፍ የአባላት ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ በበጀት አመቱ የክልሉን የመልማት አቅም በመለየት ድህነትን መቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በተለይም የእንስሳት ልማት፣ የማህበራዊ አገልግሎት፣ የቱሪዝም ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት፣ የስንዴ ልማት፣ የፍራፍሬና ሌሎችም የግብርና ልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተቀረጹ 6 ኢንሼቲቮችና 68 ፓኬጆች ከክልሉም ባለፈ እንደ ሀገር የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ጥሩ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት፣ ጉድለቶችን በመሙላትና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር በማድረስ ለሀገራዊ የብልፅግና ስኬት በጋራ መትጋት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አብረሃም ማርሻሎ በፓርቲው ጉባኤ የሰላም ግንባታና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች አጽንኦት መሰጠቱን አንስተው የክልሉ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
በመልካም አስተዳደር ዘርፉ ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በተወሰደ እርምጃ መሻሻል መኖሩን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የሃሳብ ብዝሃነትን በማክበርና የልማት አንድነትን በማጠናከር በተለይም በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታትና የማስተካከል ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ በ2017 እቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ እቅድ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አደረጃጀቶችም እውቅና ተሰጥቷል፡፡