ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ቀጣናዊ የልማት ትብብር ማስተሳሰሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የሀገራቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቀጣናዊ የልማት ትብብር ማስተሳሰሪያ ገመድ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር “የባቡር መሠረተ ልማት ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሃሳብ እ.አ.አ. ከ2025 እስከ 2028 የሦስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ የፓናል ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

ሚኒስትሩ በመክፈቻ መልዕክታቸው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ለሀገራዊና ቀጣናዊ ልማት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መሠረተ ልማትም የቀጣናዊ ትስስር መገለጫ ሆኖ መዝለቁን ተናግረዋል።

በቀጣይም የባቡር መስመሩን ፍጥነት መጨመር የሚያስችሉ ተጨማሪ መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያና ጁቡቲ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው የባቡር መስመሩም ለንግድ፣ ለትራንስፖርት ለቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ የመተሳሰሪያ ገመድ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የመተላለፊያ ጊዜን በመቀነስና አቅምን በማሳደግ ቀጣናዊ ውህደትና የልማት ትብብርን በማስፋት የንግድ ሥርዓትን እያቀላጠፈ መሆኑን አንስተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎትን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው የከተማና ገጠር አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ደኅንነት ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በተሻለ ፍጥነት በማጓጓዝና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ሥርዓትን እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ሂደት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የባቡር መስመሩ በቻይና መንግስት የአንድ መንገድ የአንድ ቀበቶ (ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት) መገንባቱ የሶስቱን ሀገራት ስኬታማ የልማት ትብብር የሚሳይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎትን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የባቡር መስመሩ የኢትዮ-ጅቡቲን የልማት ተጠቃሚነት በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

በከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የተገነባው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር መስመር የወጪና ገቢ ንግድ ሥርዓትን በማሳለጥ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታከለ ዑማ የባቡር መሠረተ ልማቱን የአሰራር ሥርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን የሚስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የአክሲዮን ማኀበሩ የአሰራር ሥርዓት መዘመን የሀገራቱን ተጠቃሚነት እያሳደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱም የኢትዮ-ጅቡቲን የልማት ተጠቃሚነት በማቆራኘት በትውልድ ቅብብሎሽ እየተገነባ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

በአክሲዮን ማኅበሩ ከ2025 እስከ 2028 የሦስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያና የጅቡቲ መንግስታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በስራ አፈፃጸም የተሻለ ስኬት ላስመዘገቡ ባልደረቦች ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም