ቀጥታ፡

ከተሽከርካሪ የሚወጣ የበካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የተቋማት ዝግጁነት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ከተሽከርካሪ የሚወጣ የበካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የተቋማት ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያ አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መመሪያው የአየር ብክለትን ለመቀነስ፣ የነዳጅ ወጪን ለመቆጠብ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር በሚከናወኑ ስራዎች ፋይዳው የጎላ ነው።

የበካይ ጋዝ ልቀት በጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያሰችላልም ብለዋል ።

መመሪያው በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የወጣውን ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ደረጃን ለመተግበር  የሚያስችል መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። 

በመመሪያው መሰረት ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መስፈርት በካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂን በተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም አስገዳጅ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ (ቦሎ) ምርመራ ወቅት በወጣው የኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ መሠረት ደረጃውን ማሟላቱን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት የመያዝ ግዴታ መኖሩንም አክለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት በሁሉም ተሽከርካሪዎች  ላይ በካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂን ማስገጠምና የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ ምርመራ ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑም አሳስበዋል።


 

በውይይቱ የተሳተፉ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ከበካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂዎች ጥራትና ደረጃ፣ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አቅምና ዝግጁነት አንጻር ጥያቄዎችን አንስተዋል።


 

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሃዲስ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ ምርመራ ስራውን ለማከናወን የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።

 ሆኖም  መመሪያው ላይ የተቀመጡ መሰፈርቶችን ያሟሉና በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ለማንኛውም ተቋም ዘርፉ   ክፍት ነው ብለዋል።

በተቀመጡት መሰፈርቶችና ግዴታዎች መሰረት ተጠያቂነትና ሀላፊነት በመኖሩ ከቴክኖሎጂ ጥራትና ደህንነት ጋር በተያያዘ ስጋቱን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በርኦ ሀሰን በሰጡት ማጠቃለያ መስፈርቶቸን ላሟሉ ተቋማት እውቅና የመስጠት ስራ  እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚሰማሩ ተቋማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው ኢንደስትሪውን ዝግጁ ከማድረግ አንጻርም ክትትልና ቁጥጥር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም