ኢትዮጵያን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወከሉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን እያካሄዱ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወከሉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን እያካሄዱ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወከሉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን እያካሄዱ ይገኛል፡፡
ሻምፒዮናው ከመስከረም 3 እስከ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በጃፓን ቶኪዮ ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 ሀገራት የተወጣጡ ከ2000 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ሁነት በ49 የውድድር አይነቶች ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን ለሚወክሉ አትሌቶች ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ጥሪ የተደረገላቸው አትሌቶች በብሄራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ) በሚገኘው የመሮጫ መም ላይ ዝግጅታቸውን ከሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ እያደረጉ ይገኛል።
የመሮጫ መሙ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ባሟላ ሁኔታ መሰራቱን የፌደሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
የልምምድ ስፍራው አትሌቶች ለረጅም ጊዜ ይገጥማቸው የነበረውን የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግርን ምላሽ የሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
የቀሩ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የልምምድ ስፍራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ እንዲሳተፉ በሴቶች 27 በወንዶች 23 በድምሩ 50 አትሌቶች ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ከነዚህም ውስጥ 12ቱ ተጠባባቂ ናቸው።
አትሌቶቹ የተመረጡት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮታ፣ ባሟሉት ሰዓት (ሚኒማ) እና በቀጥታ ተሰላፊ በመሆን ነው።
በ10000 ሜትር ሴቶች አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ እና በሴቶች ማራቶን አትሌት አማኔ በሪሶ እ.አ.አ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ አሸናፊ በመሆናቸው ያለ ምንም ማጣሪያ በቀጥታ አልፈዋል።