በውጭ ሃገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ዕድገት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሃገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ዕድገት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል
ድሬዳዋ፣ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦በውጭ ሃገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ዕድገት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ።
ከሐምሌ 21 እስከ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም የተካሄደው የ''ናፍቆት ድሬደዋ'' ዓመታዊ በዓል አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ዕውቅና በመስጠት ዛሬ ተጠናቋል።
በዓመታዊው በዓል ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀት እና ሌሎች ሽልማቶች የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ሰጥተዋል።
የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በውጭ ሃገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እና በልማት ስራዎች ላይ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ በመሳተፍ፣የአረጋውያንን ቤቶች በመጠገንና ማዕድ በማጋራት እንዲሁም ለኩላሊት እጥበት ማዕከል የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ለእነዚህ አበረታች ስራዎች መጠናከር ዓመታዊው የ''ናፍቆት ድሬደዋ'' በዓል አንድነትና ትስስርን በማጠናከር ረገድ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እያበረከቱ ለሚገኘው አስተዋፅኦ ከንቲባው አመስግነው በቀጣይም በአገርና በከተማዋ የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ የተሻለ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የ''ናፍቆት ድሬደዋ'' ዓመታዊ በዓል አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፥ የዘንድሮው በዓል የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነትን በማፅናት በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ለበዓሉ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዳያስፖራ ማህበረሰብ እና የተለያዩ አጋር አካላት አስተዳደሩ ያመሰግናል ብለዋል።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአገሩ በተለይም በድሬዳዋ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ በመሰማራት ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን ይበልጥ እያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በማኑፋክቸሪንግ፣በሆቴልና ቱሪዝም፣በንግድ እና በሌሎች ዘርፎች በመሰማራት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ለሃገር ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።