ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የቅንጅት ስራ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የቅንጅት ስራ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2017 (ኢዜአ)፦ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያ አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መመሪያው የአየር ብክለትን ለመቀነስ፣ የነዳጅ ወጪን ለመቆጠብ፣የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር በሚከናወኑ ስራዎች ፋይዳው የጎላ ነው።
የበካይ ጋዝ ልቀት በጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያሰችላልም ብለዋል ።
መመሪያው በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የወጣውን ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ደረጃን ለመተግበር የሚያስችል መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በመመሪያው መሰረት ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መስፈርት በካይ ጋዝ ልቀት መቀነሻ ቴክኖሎጂን በተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም አስገዳጅ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ (ቦሎ) ምርመራ ወቅት በወጣው የኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ መሠረት ደረጃውን ማሟላቱን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት የመያዝ ግዴታ መኖሩንም አክለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥር መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሃዲስ በበኩላቸው፥ ከትራንስፖርት ዘርፉ 20 በመቶ የሚሆነው የልቀት ድርሻ የሚይዘው ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ ልቀት ነው ብለዋል።
ተሽከርካሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርጉትን አሉታዊ ተጽዕኖ መቆጣጠር በማስፈለጉ መመሪያው ወጥቷል ብለዋል፡፡
በመመሪያው በመላ አገሪቱ በሚገኙ ተሽከርካሪዎች፣ ገጣጣሚዎች፣ በመላ አገሪቱ በሚንቀሳቀሱ በተሽከርካሪ አምራቾች እና አስመጪዎች፣ እንዲሁም በተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ማሟላት ያለባቸውን መሰፈርቶችና ግዴታዎች መካተቱን አብራርተዋል።