በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመር የሚያስችል ውይይት ተካሔደ

መቀሌ፤ ሀምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አድርገናል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከዝግጅት ምእራፍ አንስቶ በሂደት የምክክር ምእራፍ ላይ ይገኛል።

የእስከ አሁኑ ሂደትም አሳታፊ በሆነ መልኩ የተከናወነ መሆኑንና በስኬታማነት መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

የምክክር ኮሚሽኑ የጀመረውን ስኬታማ ጉዞ በመቀጠልና ተሞክሮዎችን በመቀመር በትግራይ ክልልም ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በክልሉ የተጀመረው እንስቅስቃሴ ምን ይመስላል? በማለት ኢዜአ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን አነጋግሯል።

ኮሚሽነሩም በማብራሪያቸው የምንም ነገር መፍትሄው ምክክር መሆኑን አንስተው ለኢትዮጵያ አሁን ላይ ከምንም በላይ ምክክር ያስፈልጋታል፤ ይህንንም በነፃነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ ቀጥለንበታል ሲሉ ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች አሳታፊና አካታች የሆነ አጀንዳ የማሰባሰብና የልየታ ስራ በተሳካ መልኩ መካሄዱን አስታውሰው በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ መልኩ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አረጋግጠዋል ።

በመሆኑም በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ሌሎች አካላት ጋር አድርገናል ብለዋል።

በውይይታቸውም ለሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ሌሎች ስራዎች አጋዥ የሚሆኑ ገንቢ የውይይት ጊዜ እንደነበራቸው ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ ለስኬታማነቱ እገዛና ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የምክክሩ ሂደት በሌሎች አካባቢዎች በነፃነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ገልፀው በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ መልኩ የሚካሄድ በመሆኑ ሁሉም አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን ለማጥበቅና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት የሚያስችል በታሪክ አጋጣሚ የተገኘ እድል መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም