ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ታግዛለች - ኢዜአ አማርኛ
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ታግዛለች

ባሕርዳር ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ) ፡- ባሕርዳር ከተማ የደረሰችው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታግዛለች ሲሉ የአማራ ክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ አስታወቁ።
የጣናነሽ ቁጥር፪ ጀልባ ዛሬ ባሕርዳር ከተማ ደርሳለች ።
ከጅቡቲ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች በማቆራረጥ ባሕርዳር የደረሰችው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የተገዛች ናት።
የጀልባውን አገልግሎት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም እንዳመለከቱት፤ የጀልባዋ መምጣት የቱሪስቶችን ደህንነት በመጠበቅና በተሻለ ፍጥነት በመጓጓዝ በጣና ሃይቅ ውስጥ ያሉ የመስህብ ሃብቶች ለመጎበኝት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።
በጣና ሃይቅ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ገዳማትና ታሪካዊ ቅርሶች ፣ አድባራት፣ ብዝሃ ህይወትና ሌሎች የመስህብ ሃብቶችን በመጎብኘት ጸጋዎችን ለማወቅና ለማሳወቅ ሰፊ እድል ትፈጥራለች ብለዋል።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከባሕርዳር ተነስተው ወደ ጎርጎራ ሪዞርት፤ ከዛም ወደ ጎንደርና ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሂደው ለመጎብኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የባሕርዳርና የጎንደር አካባቢዎችን በፈጣን የውሃ ትራንስፖርት በማስተሳሰር የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ አቶ መልካሙ አስረድተዋል።
በቅርቡም እስከ 35 ሰዎች የሚይዙ አምስት ፈጣን ጀልባዎች ወደ ጣና ሃይቅ ገብተው ለጎብኝዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አውሰተው፤ የጣናነሽ ቁጥር፪ መምጣት ደግሞ ባንድ ጊዜ ቁጥሩ የበዛ ሰው ለማጓጓዝ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
ለቱሪዝም ልማት ዋናው የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ወሳኝ ነው ያሉት አቶ መልካሙ ፤ በቀጣይም ፈጣን ጀልባቸውን በማስገባት የቱሪዝም ልማቱን ለማፋጠን ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የጣናነሽ ቀጥር ፪ መምጣት በዘርፉ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂና ደህንነት ከፍጥነት ጋር ይዛ የመጣች በመሆኑ በባሕርዳር ላይ ለሚደረገው ጉዞ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሕርዳር ከተማ የተገነባው የኮሪደር ልማት የጣና ሃይቅን በመግለጡ ህዝቡ በሁሉም አቅጣጫ ሃይቁን የመጎብኘት እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ይህም የፈጣን ጀልባዎች መምጣት ጋር ተዳምሮ የአካባቢውን ገጽታ ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ከጅቡቲ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች በማቆራረጥ ዛሬ ባሕርዳር ከተማ የደረሰችው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የተገዛች ስትሆን፤ በጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት እንደምትሰጥ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ የመጀመሪያዋን ጣናነሽ ጀልባ ጨምሮ እንደ ፋሲለደስና ንጋት ያሉ ከፍተኛና መካከለኛ ጀልባዎች በሃይቁ ላይ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተመልክቷል።