የኢትዮጵያ አረንጓዴ ማዕበል

ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ሀገር ናት። ትጋት፣ አይበገሬነት እና ጽናትን የማንነት ካባቸው አድርገው የለበሱ ዜጎቿ ፊታቸው ካለው ችግር ይልቅ የነገን መጻኢ ብሩህ ተስፋ እያዩ በአንድነት በመጓዝ በስኬት ላይ ስኬት በድል ላይ ሌላ ድል በገድል ላይ አዲስ ገድል እያስመዘገቡ ኖረዋል። አሁንም በዚህ ብርቱ የድል አድራጊነት መንፈስ ቀጥለዋል። ለማሳያነት አትሌቲክስን እንመልከት። ከኢትዮጵያ የተለያዩ መልክዐ ምድሮች የፈለቁ አትሌቶች ድል ከማስመዝገብ ባለፈ መልካም ገጽታዋን ገንብተዋል። ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል። ስሟን አስጠርተዋል። ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት የሚለውን እሳቤ ከንግግር ባለፈ በተግባር አሳይተዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከድላቸው ጀርባ አንድ ትልቅ ኃይል አለ የቡድን ስራ ይባላል። አትሌቶች ከግል ክብራቸው ይልቅ ሀገርን በማስቀደም በቡድን ስራ የሚያስመዘግቡት ድል “አረንጓዴው ጎርፍ” (Green Wave) የሚል ታዋቂ ስያሜ አሰጥቷቸዋል። አረንጓዴው ጎርፍ ኢትዮጵያውያንን በደስታ ጮቤ አስረግጧል ሀሴት እንዲሰማቸው አድርጓል። ይህ የአረንጓዴ ማዕበል መንፈስ ከአትሌቲክስ መሮጫ መም እና ሜዳ ወደ ደኖች፣ ኮረብታዎች እና እርሻ ስፍራዎች ሰተት ብሎ ገብቷል። በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ሰባተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል። ትናንት በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ 700 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 714 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ተሰርቷል። በዚህ አኩሪ ስራ ላይ 29 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች መሳተፋቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። አትሌቶች በመሮጫ ስፍራው የብሄራዊ አይበገሬነት እና ክብር ምልክት ሲሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥቶ ችግኝ በመትከል የደን መልሶ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ አሸናፊ ሆነዋል። ሚሊዮኖች ችግኝ ሲተክሉ ልክ እንደ አትሌቶቹ አንድነት፣ ጽናት እና አላማን በቁርጠኝነት ማሳካትን አሳይተዋል።

አፍሪካን ኒውስ የትናንቱን የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አስመልክቶ በሰራው ዘገባ  በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እና ደንን ለመጠበቅ አረንጓዴ ማዕበል ሆነው ችግኝ ተክለዋል ሲል አድናቆቱን አስፍሯል። ዘገባው ኢትዮጵያውያን ያሳዩትን አንድነት እና ህብረት አሞካሽቷል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን በነቂስ ወጥተው ችግኝ ይተክላሉ? ለሚለው ጥያቄ ከፊት ለፊት የሚመጣው ምላሽ ችግኝ መትከል ለከባቢ አየር ጥብቃ አንገብጋቢ አጀንዳ ከዛ ሲያልፍም ማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመፍታት ቁልፍ ነው ብለው በጽኑ ስለሚያምኑ ነው። ማህበረሰባዊ መሰረት በያዘው አረንጓዴ አሻራ ዜጎች በመትመም ለችግኝ ተከላ የሚወጡት በጉዳዩ ላይ የባለቤትነትና የኃላፊነት ስሜት ስለሚሰማቸው ነው።

አረንጓዴ አሻራ በርካታ ትሩፋቶችና በረከቶች ያሉት ነው። የኦክስጅን አቅርቦት ጨምሯል፣ የአየር ንብረት ሚዛንን ጠብቋል አልፎም የተራቆተ መሬት መልሶ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እያደረገ ይገኛል። ደኖች የአፈር ለምነትን በማሻሻልና ውሃን አቅቦ በመያዝ የምግብ ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ከዚህ አንጻር አረንጓዴ አሻራ ያለው ሚና ግዙፍ ነው። ምርታማ የሆነ መሬት ሲሰፋ እና ስነምህዳሮች ከጉዳታቸው ታክመው ነባር ይዞታቸውን ሲይዙ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጥ፣ አይበገሬ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባትና አካባቢን የመጠበቅ ህልሟን ያሳካል።

አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የተሻገረ ትርጉም ያለው ነው የአንድነት እና የብሄራዊ ክብር መገለጫም ሆኗል። ኢትዮጵያውያን ለአንድ አላማ ከቆሙና ከተባበሩ ከስኬት ማማ ለመድረስ የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ በግልጽ አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት በአንድ ጀንበር የ700 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በሰጡት አስተያየት አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ትላልቅ ዕቅዶችን አቅዳ ህዝቧን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ትልቅ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው መሳተፋቸው የሀገርን የጋራ ራዕይ ለማሳካት ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከሀገር ያለፈ ቀጣናዊ አንድምታ አለው። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በስጦታ በማበርከት ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ከፖሊሲ ትኩረት ባለፈ በተግባር አሳይታበታለች። ኢትዮጵያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከሏ የቀጣናው ፈተና የሆነውን ድርቅን በመከላከል፣ ጎርፍን በመቀነስ እና ስነ ምህዳር እንዲያገግም በማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ላይ ለተገኙት የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ የአራት ሺህ ችግኞች ስጦታ ማበርከታቸው የሚታወስ ሲሆን በምላሹም ናይጄሪያ ለኢትዮጵያ 2 ሺህ የካሽው ችግኝ እና 100 ሺህ ዘር በሥጦታ አበርክታለች። ይህ አረንጓዴ አሻራ የፓን አፍሪካን የአጋርነት መንፈስ አዲስ መገለጫ እና ጉዳዩ የአፍሪካ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን አመላካች ሲሆን አፍሪካውያን በአካባቢ ጥበቃ ዘላቂ ትብብር መፍጠር እንዳለባቸውም የሚያስገነዝብ ነው።

እዛው አፍሪካ ላይ ስንቆይ አረንጓዴ አሻራ ከአፍሪካ ህብረት ትልቁ ማዕቀፍ አጀንዳ 2063 ጋር የሚጎዳኙ ጉዳዮች አሉት። አጀንዳ 2063 የበለጸገች እና አረንጓዴ አፍሪካን እውን ሆኖ የማየት ህልምን ያነገበ ነው። በደን መልሶ ልማት እና ዘላቂ ግብርና ስራ የመሪነት ሚና እየተወጣች የምትገኛው ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2063 ቁልፍ ግቦች መካከል ለስነ ምህዳር መልሶ ማገገም፣ ሁሉን አቀፍ ልማት እና ቀጣናዊ ትብብር ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች። የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ አጀንዳ 2063 በእሳቤ ደረጃ ሊያሳካቸው ያሰባቸውን ጉዳዮች በተግባር የገለጠ ተምሳሌት ነው ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ከፍታ ጨምሯል። በቅርቡ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ያከናወነቻቸውን ስራዎች ለዓለም በስፋት አስተዋውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ገንቢ ሚና እየተወጣች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሁነት የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች ያጎላች ሲሆን በአረንጓዴ አሻራ ሀገር በቀል ኢኒሼቲቭ በትብብር እና ፈጠራ በታከለባቸው የመፍትሄ አማራጮች ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ግቦች ማሳካት እንደሚቻልም አሳይታለች። የጉባኤው ተሳታፊዎችም በአረንጓዴ አሻራ ላይ መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ችግኝ ተክለዋል። ይህ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ በተግባር ፍንትው ብሎ የታየበት ነው።

አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት  ለውጥን ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የከባቢ አየር መራቆትን ለማስቀረት ስራዎች ዓለም አቀፍ ተምሳሌት የሚሆን ነው። ኢኒሼቲቩ እንደ ኢትዮጵያ ያለች በማደግ ላይ የምትገኝ ሀገር በራዕይ እና በተግባር በመምራት ሌሎች ሀገራት የህዝብ ኃይልን ተጠቅመው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ያነሳሳል። አረንጓዴ አሻራ መንግስት እና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው መጻኢው ጊዜ ብሩህ የሆነና አረንጓዴ የለበሰች ሀገር ለመፍጠር ቆርጠው ከተነሱ የማይሳካ ነገር እንደሌለም አመላካች ነው።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የእስከ አሁን ቆይታ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች። አረንጓዴ አሻራ ቀጣይነት ያለው እና የረጅም ጊዜ ብሄራዊ ተልዕኮ እና ግብ ነው። አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ የታሪክ አሻራ አካል ይሆናል ያሉት ሀሳብም የፕሮጀክቱን ዘላቂነት እና ቆይታ በግልጽ የሚያመላክት ነው።

ኢትዮጵያ ትናንት በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ ለምትካል አቅዳ 714 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል ከእቅድ በላይ አሳክታለች። በ2018 ዓ.ም በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን ብዛት 50 ቢሊዮን የማድረስ እቅድ ከእቅድ በላይ በላቀ ሁኔታ እንደሚሳካ ሳይታለም የተፈታ እውነት ነው።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት ትላልቅ ህልሞቿን፣ እቅዶቿ እና ራዕዮቿን ማሳካት እንደምትችል በግልጽ አሳይታለች።  በአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ በመስጠት፣ የተፈጥሮ ጠበቃ በመሆን እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ጉዞ ዘላቂ መሪነቷን እያሳየች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም የአረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን አሸናፊ እና ቁንጮ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው። ለግዙፍ ሀገራዊ አላማ በሚሊዮኖች ደረጃ የሚተመው አረንጓዴ ማዕበልም ይህን ግብ የሚያሳካ ትልቅ ሀብት እና አቅም ሆኖ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም