የባሕርዳር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጣናነሽ ቁጥር ሁለት ጀልባን ለመቀበል አደባባይ ወጥተው እየተጠባበቁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባሕርዳር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጣናነሽ ቁጥር ሁለት ጀልባን ለመቀበል አደባባይ ወጥተው እየተጠባበቁ ነው
ባሕርዳር ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፡- የባሕርዳር ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች ጣናነሽ ቁጥር ሁለት ጀልባን ለመቀበል በጊዮርጊስ አደባባይና በከተማው ዋና ጎዳናዎች ወጥተው እየተጠባበቁ ነው።
ነዋሪዎቹ ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባን የሚያወሱ የተለያየ መልእክት ያላቸውን ባነሮች በመያዝና በባሕል አልባሳት በመድመቅ ነው ለአቀባበሉ የወጡት።
ጀልባዋ ባሕርዳር ከተማ እንደገባች በዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር ለሕዝቡ እይታ በመቅረብ ወደ ተዘጋጀላት የአቀባበል ቦታ ጊዮርጊስ አደባባይ አካባቢ እንደምታመራ ይጠበቃል።
በአቀባበሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአማራ ክልል እና የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በመገኘት መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የጀልባዋን አቀባበል ሁኔታ እየተከታተለ ወቅታዊ መረጃ የሚያደርስ ይሆናል።
ከጅቡቲ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች በማቆራረጥ ዛሬ ባሕርዳር ከተማ እንደምትደርስ የምትጠበቀው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የተገዛች ስትሆን፤ በጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት እንደምትሰጥ ይጠበቃል።