በሲዳማ ክልል ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 25/2017 (ኢዜአ)፡ - በሲዳማ ክልል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጎለብቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2017 ክልል አቀፍ የአባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኮንፍረንሱ የተዘጋጀው "ጠንካራ አደረጃጀት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በኮንፍረንሱ ላይ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስትና ፓርቲ በመቀናጀት ያከናወኑት ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝተዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታትም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ፓኬጆች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል።
ከዚህም የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጅ እንደሚገኝበት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዜጎች በትንሽ ቦታ ላይ አዋጭ በሆኑ የግብርና ስራዎች ላይ በመሳተፍ ኑሯቸው መሻሻሉን ተናግረዋል።
በመንገድ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የተሄደበት ርቀትም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ በየዘርፉ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
በመድረኩ የፓርቲው ስነ ምግባርና ኢንስፔክሽን ፣ ዓመታዊ እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የተመለከተ ሲሆን፤ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አደረጃጀቶችም እውቅና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።