ሆስፒታሉ ከለውጡ በፊት የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየረ ስራዎችን እውን አድርጓል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታሉ ከለውጡ በፊት የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየረ ስራዎችን እውን አድርጓል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2017(ኢዜአ)፦ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል ከለውጡ በፊት ታካሚዎችን ለእንግልት ሲዳርግ የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየረ ስራዎችን አሁን እውን አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል የለውጥ ስራዎችን ጎብኝተናል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከለውጡ በፊት ታካሚዎችን ለእንግልት ሲዳርግ የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት የቀየረ ስራዎችን አሁን እውን አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይ ለታካሚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያዘምኑ የጤና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተመልክተናል ነው ያሉት።
ሆስፒታሉ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችና ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል ደረጃውን የጠበቀ እና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ የአገልግሎት ማሻሻያና የማስፋፊያ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የሆስፒታሉ አረንጓዴ ምድረ ግቢ ለህክምና አገልግሎት የሚመችና ፅዱ የሥራ ከባቢ እንዲፈጠር ማድረጉንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጅግጅጋ ከተማ ሁሉን አቀፍ እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ የተቋም ግንባታ እያከናወኑ የሚገኙትን የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን አይተናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡
ተቋማቱ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በቢሮ እድሳት አስደናቂ ለውጥ ላይ እንደሚገኙም ተመልክተናል ብለዋል፡፡