ቀጥታ፡

"የጽዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ ህብረተሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ እያሳደገው ነው - ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ

አሶሳ፤ሐምሌ 25/2017 (ኢዜአ)፦ "የጽዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ  ህብረተሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ እያሳደገ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ አስታወቁ።

"ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ 2ኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ማስጀመሪያ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል።


 

መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ እንደገለፁት የጽዱ ኢትዮጵያ መርሃ ግብር ለነዋሪዎች  ጤናማ እና ንፁህ አካባቢ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ የሚገኘው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መድረክ ህብረተሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ  እያሳደገ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች የጽዱ ኢትዮጵያ አካል መሆናቸውን ገልፀው አካባቢያችንን ንፁህ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ጽዱ ኢትዮጵያ ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን በማዘመን ውብ እና ንፁህ አካባቢ እንዲፈጠር የሚያግዝ ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር እንደሆነም አንስተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ንፁህ አካባቢን ለትውልድ ማስተላለፍ ስለሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት።


 

የክልሉ መንግስት እንደ ሀገር የተያዘው መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን የጀመራቸውን የአረንጓዴ ቦታዎች ማስፋፋት እና ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲዘረጋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉ እና የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም