በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማስጠበቅ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል- አፈ-ጉባዔ መሰረት ማቲዎስ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማስጠበቅ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል- አፈ-ጉባዔ መሰረት ማቲዎስ

ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 25/2017 (ኢዜአ) ፡- በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማስጠበቅ በህዝቡ ለሚነሱ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎች ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 4ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሁሉም በአንድነት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል።
በተለይም ህዝቡን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ጫና ለማርገብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሌላው በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ በክልሉ የታለሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በማድረግ የህዝቡ የልማት ፍላጎቶች ምላሽ እንዲያገኙ ያለሰለሰ ጥረት ማድረጉን አውስተዋል።
በቀጣይ የተጀመሩ የድጋፍና የክትትል ስራዎችን በማጠናከር በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ምክር ቤቱ በትጋት ይሰራል ብለዋል።
ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታ የክልሉን የ2017 የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የእቅድ ክንውን ሪፖርት አዳምጦ ውይይት በማድረግ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
እንዲሁም የ2018 እቅድ፣ የማስፈጸሚያ በጀት፣ አዋጆችንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የድርጊት መርሃ ግብሩ ያመለክታል።
በጉባኤው ላይ ከምክር ቤቱ አባላት በተጨማሪ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ አመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።