የነገን ተስፋ ያጸኑ ታዳጊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የነገን ተስፋ ያጸኑ ታዳጊዎች

ትንንሾቹ ልጆች እየተራወጡ የሚተክሏቸውን ችግኞች ያነሳሉ። ዓይኖቻቸው ጉድጓድ ይፈልጋሉ። ባገኙት ቦታ ላይ ለመትከል ትናንሽ እጆቻቸውን ከአፈር ጋር ያዋድዳሉ። በትናንሽ ጣቶቻቸው የሚጭሩት አፈር የነገ ታሪክ ድርሳናቸው ማበልጸጊያ ነው። ልጆቹ ችግኝ መተከልን የእነርሱንና የመጪውን ትውልድ ነገ ምቹ የማድረግ ታላቅ ፕሮጀክት አካል ስለመሆኑ መረዳታቸውን ሲናገሩ ይደንቃሉ።
ዛሬ ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ተተክሎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ እንክብካቤ እንደሚደረግለት በራሳቸው አንደበት ይመሰክራሉ፤ ልክ እንደነሱ እንክብካቤ እንደሚጠይቅ ያምናሉ።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት ከሰባት ዓመታት በፊት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የዘንድሮውን ጨምሮ በድምሩ ከ47 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ከመገንባት በላይ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ እንደሀገር በአንድ ጀንበር ባካሔደችው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከህጻን እስከ አዛውንት በመሳተፍ 714 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ያቀደችውን አሳክታለች።
በዚህ ስኬት ውስጥ በትናንሽ መዳፋቸው ችግኝ ይዘው፤ በትናንሽ ጣቶቻቸው አፈር ያለበሱ ድንቅ ሕጻናት አሉ።
ኢዜአ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነጋቸውን ሲተክሉ ያገኛቸውን ሕጻናት የነገ ተስፋቸውን ሊያሳምሩ ሲታትሩ አነጋግሯቸዋል።
ህጻናቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ነጋችን በተስፋ እንዲሞላ ከማድረጉ ባለፈ ሀገራችን ምቹና ለትውልድ ተስፋ እንድትሆን የሚያደርግ ነው ሲሉ ለዛ ባለውና በሚጣፍጥ አንደበታቸው ይገልጻሉ።
የሚተከሉት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉና ፍራፍሬ በመሆናቸው እኛ ታዳጊዎች በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር እንድንረከብና የተመጣጠነ ምግብ አግኝተን እንድናድግ ያደርጋል ይላሉ።
ችግኞቹ በጤናማ የአየር ንብረት ቦርቀን ለማደግ የሚረዳ ሲሆን፤ ለቀጣዩ ትውልድም የተስተካከለች ሀገር እንድናስረክብ እድሉን የሚከፍት ነው ብለዋል።