ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለሌሎች አገራትም በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የሱዳን ስደተኞች

አሶሳ፤ ሐምሌ 24/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለሌሎች አገራትም በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ተናገሩ።

የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃግብር በክልሉ ባምባሲ ወረዳ ስደተኞች መጠለያ አካባቢ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም የሱዳን ስደተኞች ተሳትፈውበት ተከናውኗል።


 

በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለሌሎች አገራትም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ጣሪቅ ሀሰን የተባሉ የሱዳን ስደተኛ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልፀው፥ ይህን የኢትዮጵያ ተሞክሮ ሁሉም ሊደግፈው የሚገባና ዓለም አቀፍ አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ድርቅን ለመቋቋም እና የአየር ንብረትን ለማስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ሁሉም ሀገራት ሊተገብሩት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌላው ሱዳናዊ አጀሊ ሰቢት በበኩላቸው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከትልልቅ የሀገሪቱ መሪዎች ጀምሮ የተሰጠው ትኩረት እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።


 

ችግኝ መትከል የአካባቢ ስነ ምህዳር እንዲጠበቅ ከማድረጉም በላይ የተተከሉ ችግኞች በሚደረግላቸው እንክብካቤ ፍሬ እየሰጡ እና የደን ሽፋን እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስደተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ መሳተፋቸው የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ያካተተ የልማት ስራ እያከናወነ መሆኑን ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች አገልግሎት የአሶሳ ቅርንጫፍ ተተኪ ኃላፊ ግሬስ አቲም ናቸው።


 

መርሃግብሩ የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ስደተኞችን ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በተግባር የሚያሳይ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም