የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እያከናወነች ያለው ተግባር የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።
በመላው ኢትዮጵያ ዛሬ የአረንጓዴ ዐሻራ አካል በሆነው የአንድ ጀንበር መርሃ ግብር 700 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ ከአጋር የልማት ድርጅቶች እና የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በጋራ በመሆን በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ አሳርፈዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ ዐሻራ ጥልቅ ሀገራዊ ዓላማ የያዘ ነው።
በዛሬው እለት ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መነሳቷን ጠቅሰው ይህም ቁጥር ብቻ ሳይሆን ጽናት እና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን የምናስተላልፍበት ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከዘመቻ በላይ መሆኑን ገልጸው የአካባቢ መራቆትን ለመቀልበስ ቁርጠኛ መሆናችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ በአርአያነት ለመምራት ዝግጁ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ማገገማቸውን፣ የወንዞች ተፋሰስ መታደሱን፣ ሥነ-ምህዳሮች በጉልህ እንዲነቃቁና ድርቅን የመቋቋም አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አመላክተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ የአንድ ሰው ወይም የአንድ መንግሥት ሀገራዊ ሃላፊነት አለመሆኑን ይልቁንም የጋራ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነው ብለዋል።