ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራና መሰል የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት መሰረት እየጣሉ ነው-ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር )

ታርጫ፤ሐምሌ 24/2017 (ኢዜአ)፦በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና መሰል የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት መሰረት እየጣሉ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር ) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ ጎሪቃ በርሳ ቀበሌ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን አስጀምረዋል።


 

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ህዝብና መንግስት በቅንጅት የሚያከናውኗቸው የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ልማቶች ለኢትዮጵያ  ማንሰራራት  መሰረት እየጣሉ ነው።

ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውንና በዚህም የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የአፈር ለምነት እንዲመለስና  የውሃ ሀብት  እንዲያድግ  ማድረግ ተችሏል ብለዋል።


 

የችግኞቹ መተከል የአካባቢ ስነምህዳር እንዲስተካከል ከማድረግ ባለፈ የግብርና ምርታማነት እንዲያድግ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።


 

የዘንድሮው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ654 የተከላ ቦታዎች ከ7 ሺህ 924 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚያካልል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሀገር የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ብዝሀ ህይወት እንዲጠበቅ የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል።


 

መምህራንም ተማሪዎችን ከማስተማር ባለፈ ችግኝ በመትከል ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በዞኑ 181 ቀበሌዎች ከ3ሺህ 23 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ለይ የመኖ፣ የፍራፍሬ፣ የደንና ሌሎች ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ከ500 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ተከላው እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም