ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እና የተሻለ ነገን እየገነባች ነው- ዲፕሎማቶች እና የውጭ ኢንቨስተሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እና የተሻለ ነገን እየገነባች ነው- ዲፕሎማቶች እና የውጭ ኢንቨስተሮች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት በአካባቢ ጥበቃ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እና የተሻለ ነገን እየገነባች እንደምትገኝ ዲፕሎማቶች እና የውጭ ኢንቨስተሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንድ ጀንበር የ700 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ማለዳ በጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግስት አስጀምረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ሚሊዮኖች በነቂስ ወጥተው ችግኝ እየተከሉ ይገኛል።
በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሊዩ ዢያዎጉዋንግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፋቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ለመዋጋት እና ለቀጣይ ትውልዶች የተሻለ ጊዜን ለማምጣት እያደረገ ያለው የጋራ ጥረት እንደሆነም ተናግረዋል።
ቻይና የአረንጓዴ ልማት ትብብር አካል በመሆኗ ደስታ ይሰማታል ያሉት ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ሁለቱ ወገኖች በዘርፉ ያላቸው ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የካርቦን ልህቀት መቆጣጠሪያዎች ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ሌሎች ዲፕሎማቶችም አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተወጣች ያለውን የመሪነት ሚና የሚያሳይ መሆኑን አድንቀው የተሻለ ነገን ለመስራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄልፑት ችግኝ መትከል ለልጅ ልጆች የሚተርፍ ትልቅ ስራ ነው፤ ወደ ኋላ መለስ ብለው በማየት ዛሬ ላይ የተከናወነውን ስራ ያደንቃሉ ሲሉ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ኩባንያዎች ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ የሚወጡት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።
የግል ኩባንያዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከዛሬ አልፎ ለትውልድ በሚሻገረው የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ኢሼቲቮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ስቲል ፕሮፋይሊንግ እና ቢውልዲንግ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ማህዲ ዜሙቺ በአረምጓዴ አሻራ ላይ በመሳተፉ ክብር እንደሚሰማው ገልጸው የኢትዮጵያን መንግስት ጥረት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የከባቢ አየር ጥበቃን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ለመረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው፥ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።