ሰራዊቱ ከሰላም ማስፈን ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ድርብ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ ከሰላም ማስፈን ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ድርብ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ ሰራዊቱ ከሰላም ማስፈን ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ድርብ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ።
ከ11ዱም ክፍለ ከተማና ከፖሊስ ኮሌጅ የተወጣጡ የፖሊስ ሰራዊት አባላት የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራቸውን በኮልፌ ቀራንዩ ክፍለ ከተማ ወይራ ኮንዶሚኒየም አካባቢ አኑረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ከሰላምና ደህንነት ጎን ለጎን የአካበቢ ጥበቃ ስራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ነው።
የአካበቢ ጥበቃ ስራ ከሰራዊቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፣ የፖሊስ አባላት ዜጎች እንደ ሰላም ሁሉ ንፁህ አየር እንዲያገኙ አረንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፍ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለዋል።
እንደ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ ገለጻ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ አንስቶ የፖሊስ አባላት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ናቸው።
አባላቱ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ አካበቢን የመንከባከብ ድርብ ተልዕኮ እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ኮማንደር ጉማታው ገዳሙና ዕጩ መኮንን አበባ ጋሻው በበኩላቸው፥ ሰራዊቱ ባለፉት ዓመታት የተከላቸው ችግኞች ፍሬ ማፍራታቸውን ነው የተናገሩት።
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ንጹህና አረንጓዴ አገርን ለትውልድ የማስተላለፉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የ2017 ዓ.ም የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቱ ከማለዳው ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።