ቀጥታ፡

ለተከልነው ችግኝ አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ እናደርጋለን - የሀዋሳ ከተማ እና የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች

ሀዋሳ፤ሐምሌ 24/2017 (ኢዜአ)፦ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ላይ  በመሳተፍ ለተከሉት  ችግኝ   አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ  እንደሚያደርጉ የሀዋሳ  ከተማ እና የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች  ገለጹ።  

ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጀማል መሀመድ በሰጡት አስተያየት፤ የሚኖሩበት "የጫሬ ተፋሰስ" አካባቢ  የተጎዳ እንደነበር ጠቅሰው ፤ አሁን ላይ አካባቢያችን አረንጓዴ ለብሶ በማየታችን የሕሊና እርካታ አግኝተናል" ብለዋል ፡፡


 

አካባቢያቸውን አረንጓዴ ለማልበስ በየዓመቱ ችግኝ ከመትከል ባለፈ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲያደርጉ እንደቆዩ አስታውሰው፤ ዘንድሮም ለተከሉት  ችግኝ አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሌላው ተሳታፊ ታዳጊ ሕፃን የአብቃል አሸናፊ ደግሞ በተከላው በመሳተፉ ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል ፡፡


 

አካባቢያችንን አረንጓዴ ለማድረግና ጥሩ የሆነ አየር ለማግኘት መትከል አለብን ሲል አመልክቷል።

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እንዳሉት፤  የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ  አምጥቷል ፡፡


 

አካባቢዎች አረንጓዴ በመልበሳቸው በአየር ንብረት ላይ በጎ ለውጦች እየመጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃ አማራጮች በመስፋታቸውም በክልሉ በመስኖ የሚለማው መሬት  እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው፤  ከተማዋ በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም በውበትና ፅዳቷ ተጠቃሽ መሆኗን ገልፀው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ይህንን እሴት አዳብሮ ማስቀጠል ያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡


 

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገነነ ገላሳ የስራ ሃላፊዎችና የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከ44 ሺህ በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡‎


 

በተመሳሳይ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በጉራጌ ዞን  አኖር ወረዳ  "አቦጋዴ "ተፋሰስ ሕብረተሰቡን ያሳተፍ  የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ተካሄዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከልጃቸው ጋር የተሳተፉት አርሶ አደር ግዛው ድሙዴ ፤ ተክሎች የህይወት መሰረት በመሆናቸው ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር  በማሰብ ችግኝ መትከል ከሁላችን ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡‎

‎በመርሃ ግብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የሀገር በቀልና የውጭ እጽዋት ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።

‎አርሶ አደር ላቀች ንስሮ  በበኩላቸው፤ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኞች ከማዘጋጀት ባለፈ ከህብረተሰቡ ጋር በአብሮነት መትከላቸውን  ገልጸዋል።


 

‎ለችግኞቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲያደርጉ መቆየታቸውና ዛሬ ለተከሏቸውም ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

‎የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤  የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተመናመነውን የደን ሽፋን ወደ ቦታው እየመለሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


 

‎የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም  ምቹ ስነ ምህዳር የተላበሰ ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር እያስቻለ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የተተከሉ ችግኞች የተሸረሸሩ መሬቶችን በማገገም ለስራና መኖሪያ ምቹ አካባቢ ማድረግ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ ‎የጉራጌ  ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ሃላፊ አቶ እንዳለ ስጦታ  ናቸው። 

ለተከሉት  ችግኝ   አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ በማድረግ  ለማሳደግ  እንደሚሰሩም ነዋሪዎቹ  ተናግረዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም