ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስትራቴጂክ አመራሮች እና አባላት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ጀንበር የ700 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ በማስመልከት ዛሬ በሰንዳፋ በኬ ከተማ በኬ ጠቦ ቀበሌ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ችግኝ ተክለዋል።


 

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ዙሪያ እና በፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥም የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተካሄደ ያለው የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሳተፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እንደ ሀገር በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው የዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትውልድን የማሻገር እና ቋሚ ታሪክን የመትከል ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሀገር ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በምታከናውነው ማንኛውም የልማት ሥራ እየተሳተፈ ይገኛል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ።


 

በዛሬው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ የፖሊስ አመራርና አባላት ባሉበት ቦታ ሁሉ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም