ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ከተረጅነት ለመላቀቅ የተጀመረውን አገራዊ ጉዞ እንዲሳካ ሁነኛ መንገድ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ) ፦አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ከተረጅነት ለመላቀቅ የተጀመረው አገራዊ ጉዞ እንዲሳካ ሁነኛ መንገድ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላትና የዋና ጽህፈት ቤት ሰራተኞች የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአቧሬ ግንፍሌ ወንዝ ዳር አካሂደዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው አገራዊ ጥረት እንዲሳካ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፤ መንግሥትም ህዝብን በንቅናቄ በማሳተፍ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያደረገው ርብርብ ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች እና ጽዱ የሆነች አገርን ለማውረስ ቁልፍ መንገድ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ ባህል እየሆነ ህዝብም ፤በየኔነት ስሜት የሚከውነው ተግባር እየሆነ መጥቷል ብለዋል።


አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ያላት ገጽታ እንዲቀየር አወንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፥በመስኩ የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል የጋራ ርብርቡ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ተመስገን ቡርቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ አረንጓዴ አሻራ የህዝብና የመንግሥት ቁርጠኝነት እና የጋራ ድል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።


አረንጓዴ አሻራ ትሩፋቶች ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም ጭምር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት ፈዲላ ቢያ በበኩሏ፤ የዚህ ትውልድ ዓድዋ አረንጓዴ አሻራ ነው ያለች ሲሆን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው የጋራ አጀንዳ ነው ብላለች።


በመሆኑም ሁሉም አሻራውን በማኖር አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም