የኢትዮጵያን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ቁልፍ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ቁልፍ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ቁልፍ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ጅማ ላይ አስጀምረዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራርና ሰራተኞች በእንጦጦ መነ አቢቹ ክፍለ ከተማ አካኮ ወረዳ በመገኘት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለቀጣይ ትውልድ ትልቅ አሻራ የማሳረፍ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ተከታታይ አመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ማህበራዊ ሃፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የሚተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ ትኩረት ተደርጎ በተሰራው ስራ ባለፉት አመታት በባንኩ የተተከሉት ችግኞች ከዘጠና በመቶ በላይ መጽደቃቸውን አንስተዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለጤና ካለው ጥቅም በተጨማሪ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ቁልፍ ተግባራት መካከል ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል፡።
ባንኩ የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቀደም ብሎ መጀመሩን አንስተው፤ በቀጣይም ችግኝ ተከላውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የባንኩ ሰራተኞች በበኩላቸው በአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመሳተፋቸው ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ከተሳተፉት መካከል ቴዎድሮስ መስፍን እንደተናገረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ የመፍጠር ትልቅ ተግባር ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት መሰረት በሆነው መርሃ ግብር መሳተፍ የሚያስደስት መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ጥሩወርቅ ጌትነህ ነች፡፡
የዘንድሮው 7ኛ ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታልሞ በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ ይገኛል።