ቀጥታ፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር አካባቢ መልሶ እንዲያገግም የሚከናወነው ሥራ የኢትዮጵያ መገለጫ እየሆነ መጥቷል - አቶ ርስቱ ይርዳው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ) ፦ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር አካባቢ መልሶ እንዲያገግም የሚከናወነው ሥራ የኢትዮጵያ መገለጫ እየሆነ መምጣቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ለሰባተኛ ጊዜ ‹‹በመትከል ማንሰራራት›› በሚል መሪ ሐሳብ እየተከናወነ በሚገኘው በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ሀገር ዓቀፍ መርሐ-ግብር ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡


 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ርስቱ ይርዳው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት መገለጫ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ በተከታታይ በተደረጉት የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሮች ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም በተቋም ደረጃ ከ37 ሺህ በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተመጣጠነ ዝናብ ለማግኘት፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖርና በምግብ እራስን ለመቻል ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ መርሐ- ግብሩ በየዓመቱ በተነሳሽነትና በንቃት የምንሳተፍበት ሆኗል ብለዋል።

አቶ ርስቱ ይርዳው አክለውም ባለፉት 7 ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራት እንደ ሀገር በተጨባጭ የደን መመናመንን በማስቀረት ሽፋኑን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎች፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች መሳተፋቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም