የተማርነውን በተግባር ለመኖር ችግኝ ለመትከል መጥተናል - የአርባ ምንጭ ታዳጊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተማርነውን በተግባር ለመኖር ችግኝ ለመትከል መጥተናል - የአርባ ምንጭ ታዳጊዎች
አርባምንጭ ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ ስለ ዛፍ ጥቅም ያገኘነውን ዕውቀት በተግባር መኖር እንዳለብን በማመን ችግኝ ለመትከል ተገኝተናል ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ታዳጊ ህጻናት ገለጹ።
ታዳጊ ህጻናቱ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልጃቸው ጋር ችግኝ ሲተክሉ በቴሌቪዥን በማየታቸው ችግኝ ለመትከል መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል።
በመሆኑም በአርባ ምንጭ ጋንታ ተራራ ላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበትን የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ለመሳተፍ በስፍራው ተገኝተዋል።
በአርባ ምንጭ ሲቀላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ዘጸአት ታሪኩ ''ችግኝ እስትንፋሳችን እንዲቆይ የሚያግዘን የተፈጥሮ ሀብት ነው'' ብላለች።
ዛፎች ለሰው ልጆች ኦክሲጅን እንደሚያመርቱ ከትምህርት ቤት ዕውቀት መሸመቷን ጠቅሳ ችግኝ መትከል ለሰው ልጆች ህይወት ወሳኝ በመሆኑም ዛሬ ከመላው ቤተሰቤ ጋር የአንድ ጀምበር ዘመቻውን በመሳተፌ ደስ ብሎኛል ነው ያለችው።
ከወላጆች ባገኘሁት ዕውቀት መሠረት አረንጓዴ አሻራ ከተማችንን ከጎርፍ አደጋና ከደለል ይከላከላል ያለው ደግሞ የሁለተኛ ክፍል ተማሪው አብሳሎም ሙላቱ ነው።
የችግኝ ተከላው መርሃ ግብር የሚከናወነው በክረምት ወቅት እና ትምህርት ቤት ዝግ በሆነ ሰዓት በመሆኑ ከሰፈሩ ልጆች ጋር ችግኝ መትከሉን ገልጿል።
በአርባ ምንጭ ቦላ ጉርባ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሀብታሙ ማጾ እንዳለው፤ አረንጓዴ አሻራ ለጥላ የሚያገለግል በመሆኑ ከትምህርት ቤት ስንወጣ ከስሩ ቁጭ ብለን እረፍት እናደርጋለን።
ችግኝ መትከል ዝናብና ፀሐይ ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲመጡ እንዲሁም ድርቅን የሚከላከል ነው ብሏል።
አረንጓዴ አሻራ በማኖር ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተን መኖር እንዳለብን ከትምህርት ቤት ዕውቀት አግኝቻለሁ በማለትም ገልጿል ተማሪው።