የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ አካል ኃላፊነት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ አካል ኃላፊነት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ አካል ኃላፊነት ሳይሆን የጋራ የሆነ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነው ሲሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
በመላው ኢትዮጵያ ዛሬ የአረንጓዴ አሻራ አካል በሆነው የአንድ ጀንበር መርሃ ግብር 700 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ከአጋር የልማት ድርጅቶች እና የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በጋራ በመሆን በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ ጥልቅ ሀገራዊ ዓላማ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ የአንድ ሰው ወይም የአንድ መንግሥት ሀገራዊ ሃላፊነት ሳይሆን የጋራ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መነሳቷን ጠቅሰው ይህም ቁጥር ብቻ ሳይሆን ጽናት እና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገርን የምናስተላልፍበት ነው ብለዋል።
ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ማገገማቸውን፣የወንዞች ተፋሰስ መታደሱን ፣ሥነ-ምህዳሮች በጉልህ እንዲነቃቁና ድርቅን የመቋቋም አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አመላክተዋል።
መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን እድገት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ዛፎችን ስንተክል እድሎችንም እየተከልን ነው ብለዋል።