የአረንጓዴ አሻራን ከተጠቃሚነት ጋር በማያያዝ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራን ከተጠቃሚነት ጋር በማያያዝ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራን ከህዝብ ተጠቃሚነት ጋር በማያያዝ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የዘንድሮው 7ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታልሞ በመላ ሀገሪቱ ተከላው እየተከናወነ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያዊያን 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚረባረቡበት ነው፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስከ ቀጣይ ዓመት ድረስ 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መነደፉንም ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ አስታውሰው፤ የአረንጓዴ አሻራን ከተጠቃሚነት ጋር ማያያዝ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ከቡና ጋር በማያያዝም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ መላኩን ጠቁመው፤ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ የተተከሉ የቡና ችግኞች ፍሬ መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በመትከልም ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ሐሳብ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው፥ ዓመቱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት መነሻ ዓመት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
በዓመቱ ኢትዮጵያ ስኬታማ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቁመው፤ በሚቀጥለው ዓመትም ይህ ዕድገት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ከለውጡ በኋላ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ትላልቅ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም በሩዝ ልማት ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ ስንዴን ጨምሮ በሰብል ምርቶች ላይ ከፍተኛ ምርት እየተገኘበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በማዕድን ልማትም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ክልል መሆኑን ጠቁመው፤ በኮሪደር ልማትም ውጤታማ የሚባሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡