የአረንጓዴ አሻራ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችልበትን አካባቢ የሚፈጥር በመሆኑ አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችልበትን አካባቢ የሚፈጥር በመሆኑ አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ
ድሬዳዋ፤ሐምሌ 24/2017 (ኢዜአ) ፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችልበትን አካባቢ የሚፈጥር በመሆኑ አጠናክረን ልናስቀጥለው ይገባል ሲሉ የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
በድሬዳዋ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በድሬዳዋ አስተዳደር በክቡር አርቲስት ዶክተር ዓሊ ቢራ ፓርክ ተገኝተው የተለያዩ ችግኞች በመትከል ዘመቻውን ያስጀመሩት የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
በአስተዳደሩ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በወቅቱ እንዳሉት አረንጓዴ አሻራን በማኖር የተፈጥሮ ሚዛንን መጠበቅ እና መንከባከብ የሁላችንም ቀደሚ ተግባር ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰው ልጅ ንጹህ አየርና ውሃ እንዲያገኝ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር እንዲችል የሚያደርግ በመሆኑም አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ የአገራችን የማንሰራራት ጉዞ ማሳኪያና ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ወደ ብልፅግና ጎዳና ለመራመድ ለምናደርገው ጉዞ መሠረታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ በተሳሰረና በተጋመደ ወኔ እና ቅብብሎሽ ውብና አረንጓዴ የለበሰች አገር ለትውልድ የማቆየት ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ።
እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድሬዳዋን የጎርፍ አደጋ በመከላከልና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ወሳኝ ውጤቶች አስገኝቷል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከህፃን እስከ አዋቂ በተቀናጀ አንድነትና ትስስር ሁሉም የድርሻቸውን ማበርከቱን ጠቅሰው ዘንድሮም የሚተከሉትን ችግኞች በአግባቡ ተንከባክቦ ማሳደግ የሁሉም ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ የግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተተከሉት የተለያዩ ችግኞች ድሬዳዋን ምቹ የስራና የመኖሪያ አካባቢ ማድረግ አስችለዋል።
በገጠር ምንጮች ጎልብተው ለግብርና ስራ ምቹ መደላድል መፈጠሩን ጠቅሰው የአስተዳደሩን የደን ሽፋንም አሳድጓል ብለዋል።
ዘንድሮ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተገኙትን ውጤቶች ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
የዛሬው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ውሃ ገብ በሆኑ የመስኖ አካባቢዎች፣ በፓርኮች፣ በተለያዩ ተቋማት በስፋት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የካቢኔ አባላት፣ የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ናቸው።
በታሪካዊው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ ለናፍቆት ድሬዳዋ ዓመታዊ በዓል ከተለያዩ የውጭ አገራት የመጡ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።