አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ አሻራ አካል ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ አሻራ አካል ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 24/2017(ኢዜአ)፦አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ አሻራ አካል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ማለዳ በጅማ አባጅፋር ቤተ መንግስት የአንድ ጀንበር የ700 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥700 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ትልቅ እምርታ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዓለም ትልቁ የአንድ ቀን ተከላ መርሃ ግብር እንደሆነ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስምንት ቢሊዮን ገደማ ችግኝ እንደሚከተከልና ለዚህም ከስምንት ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የዚህ ዓመት ግብ ከተሳካ አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተተከለው ችግኝ ብዛት ወደ 48 ቢሊዮን ከፍ እንደሚል አመልክተዋል።
ይህም 50 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድን አንድ ዓመት እየቀረው ወደ ማሳካት እንድንቃረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ትላልቅ ነገር አስገባ፣ትላልቅ ነገር ተልማ፣ ትላልቅ ነገር አቅዳ እና ህዝቦቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ሌሎቹ ማሳያ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው መሳተፋቸው የሀገርን የጋራ ራዕይ ለማሳካት ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ ልክ እንደ ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትልቅ የታሪክ አሻራ አካል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን የድህነት ችግር እየቀረፈ የመጣና የምግብ አቅርቦት እንዲሻሻል ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ በትጋትና በጥረት ሀገራቸውን አረንጓዴ በማልበስ እና ምግብን በጓሯቸው በማምረት እና ሀገራቸውን ከችግር የማውጣት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማለዳ በጅማ አባጅፋር ቤተ መንግስት ችግኝ መትከላቸውን ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በአንድ ጀንበር ተከላ በስፋት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።