ቀጥታ፡

ሀብታም የብዝሃ ህይወት ማዕከል - ኢትዮጵያ

ሀገር በቀል ዘፎችና ዕፅዋት በጥቂቱ 

ኢትዮጵያ ለብዝሃ ህይወት ተሰማሚ ተፈጥሮ የተቸራት፣ አያሌ ሀገር በቀል እጽዋትና ዛፎች የሚገኙባት ሀገር ናት።

በዚህም በዓለም ላይ ካሉ ሀብታም የብዝኃ ህይወት ማዕከላት አንዷ ተደርጋ ትጠቀሳለች።

የተለያዩ የስነ-ምህዳር አይነቶች መገኛዋ ሀገራችን ካሏት ሀገር በቀል እጽዋትና ዛፎች መካከል ለስነ-ምህዳር ሚዛን፣ ለባህላዊ ህክምና እና ለማህበራዊ ህይወት ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸውን በጥቂቱ እንቃኝ።

ዝግባ፦ በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች በስፋት ይገኛል። ይህ ዛፍ ጠንካራና መዓዛ ያለው እንጨት ስላለው ለቤት ግንባታ፣ ለቤት ዕቃዎች መስሪያና ለተለያዩ ቁሳቁሶች በስፋት ያገለግላል። የዝግባ ቅጠል ጭማቂ በባህላዊ ህክምና በተለይ የማስመለስና የሚስቀመጥ በሽታዎችን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላል።

ወይራ፦ የወይራ ዛፍ በኢትዮጵያ ደጋማና ወይና ደጋ አካባቢዎች ይገኛል።ጠንካራና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እንጨቱም ለተለያዩ ቁሳቁሶች መስሪያነት የሚውል ነው። ፍሬውና ቅጠሉ ደግሞ ለባህላዊ ህክምና ጥቅም ላይ ይውላሉ። የወይራ ዛፍ በብዙ ባህሎች የሰላምና የጽናት ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል።

ኮሶ፦ ኮሶ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች፣ በተለይም 2000 ሜትር ከፍታ በላይ በሚገኙ ቦታዎች የሚበቅል ዛፍ ነው። የደረቁ የሴቴ ኮሶ አበባዎች  ለኮሶ በሽታ (taeniasis) በባህላዊ ህክምና በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ::  ይህም የዛፉን ስም ከበሽታው ጋር እንዲያያዝ አድርጎታል። ከህክምና በተጨማሪ ኮሶ ለአፈር ማዳበሪያነትና ለቤት ማስጌጫነትም ያገለግላል።

ሾላ፦ ጣፋጭና ተወዳጅ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ነው። በወንዝ ዳርቻዎችና እርጥበታማ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ፍሬው በቀጥታ ከመበላት ባለፈ፣ እንጨቱ ለቤት ዕቃዎች መስሪያነት ያገለግላል። የሾላ ስር ተፈልቶ ሲጠጣ ለኩላሊት ጤንነት እንደሚረዳ በባህላዊ ህክምና ይታመናል።

ዋርካ፦ ዋርካ በኢትዮጵያ ማህበራዊና ባህላዊ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ግዙፍ ዛፍ ነው። በትላልቅና ሰፋፊ ቅርንጫፎቹ ጥላ በመስጠት የሚታወቀው ዋርካ፣ ከጥንት ጀምሮ ለማህበራዊ ስብሰባዎች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች መወያያና  ለተለያዩ ባህላዊ ክንውኖች ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። ፍሬው ለምግብነት የሚውል ሲሆን፣ የተለያዩ ክፍሎቹም ለባህላዊ ህክምና ጠቀሜታ አላቸው።

ብሳና፦ ብሳና በኢትዮጵያ በስፋት ከሚገኙ ዛፎች አንዱ ሲሆን፣ የተለያዩ የመድኃኒትነት ጥቅሞች አሉት። ቅጠሉ፣ ልጡ፣ ስሩና ፍሬው ለተለያዩ በሽታዎች በባህላዊ ህክምና ያገለግላሉ። ለምሳሌ፣ የሥሩ ልጣጭ ለሆድ በሽታ፣  ቅጠሉ ለሳል፣ ፍሬው ደግሞ ለቆዳ በሽታዎች ህክምና ይውላል።

ጅብራ፦ ይህ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራማ ቦታዎች፣ በተለይም በሰሜንና በባሌ ተራሮች ላይ ብቻ የሚገኝ ግዙፍ የዕጽዋት ዝርያ ነው። ጅብራ እስከ 6 ሜትር ድረስ የሚረዝም ሲሆን፣ በአበባ በሚያጌጥበት ወቅት አስደናቂ እይታን ይፈጥራል። የራሱ የብዝሃ ህይወት ጠቀሜታ ያለው ለመድሃኒትነትም የሚያገለግል ዕጽዋት ነው።

አስታ፦ አስታ ወይም "ቅብሬቾ" በመባል የሚታወቀው ይህ እጽ፣ በኢትዮጵያ ባህላዊ ህክምና ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። በተለይም ስሩ ለራስ ምታት፣ ለጉንፋንና ለመንፈስ ችግሮች  እንደ መፍትሄ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የበለጸገ የብዝኃ ህይወት ባለቤት ብትሆንም፣ እነዚህ ሀገር በቀል እጽዋትና ዛፎች በደን መጨፍጫፍና በተለያዩ ምክንያቶች ተመናምነው ቆይተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ግን ለሀገር በቀል ዝርያዎች ትኩረት በመስጠት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመተከል ላይ ይገኛሉ። ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ መጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የኢትዮጵያውያን የጋራ ኃላፊነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም