ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለሌሎች አገሮች አርአያ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 23/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስገኘቻቸው ውጤቶች ለሌሎች አፍሪካ አገራት አርአያ መሆኑ ተገለጸ።

በአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ‘አሊያንስ ኦፍ ባዮቨርስቲ ኢንተርናሽናል ኤንድ ሲያት’ የተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት ዛሬ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሂዷል።

የተቋሙ ዳይሬክተር ጀነራል ኡያን ሉቃስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የመሪነት ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

በአገሪቱ የተመረጡና ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ ችግኞች በሰፊው እየተተከሉ መሆኑ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕጽዋትን ለማስፋፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን አርአያ እየተከተሉ መሆኑን በመጥቀስ፥ ኢትዮጵያ ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ መሆኗን እንደምትቀጥል አምናለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በተቋሙ የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካሙ ሮተንበርግ ዋንጅሩ ( ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ሌሎች አገራትም በዘርፉ ላይ እንዲሰሩ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ተሞክሮ በመላው አህጉሪቱ ሊስፋፋና ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከምታከናውነው የችግኝ ተከላ ስራና ውጤቶቹ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሊማሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በተቋሙ የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ተመራማሪ ደጀኔ ካሳሁን ( ዶ/ር) በአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተለያዩ አገራት የመጡ ሀላፊዎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአለም አቀፍ መድረኮች ከማስተዋወቅ አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

'አሊያንስ ኦፍ ባዮቨርስቲ ኢንተርናሽናል ኤንድ ሲያት' አለም አቀፍ ተቋም በአረንጓዴ አሻራ ስራዎች በአምስት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ46 ወረዳዎች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ችግኝ በተተከለባቸው አካባቢዎች የብዝሃ ህይወት ይዘት፣ ለአካባቢው እያስገኙ ያሉ ጠቀሜታዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ ስለ መርሃ ግብሩ ያለው ግንዛቤ ላይ መሰራቱን ነው የገለጹት።

በአየር ንብረት ለውጥ፣የጠፉና ደን የሚፈልጉ እንስሳት ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን እንዲሁም የደረቁ ምንጮች ወደ ተፈጥሯዊ ሁኔታቸው እየተመለሱ መሆኑን መረጃዎች ማመልከታቸውን አብራርተዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ችግኝ የመትከል ልምድን የሚያስቀጥል ጠንካራና አዎንታዊ አመለካከት መጎልበቱንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም