ቀጥታ፡

አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸውን የሰበር ውሳኔዎች በኤሌክትሮኒክስ አማራጮች ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 23/2017(ኢዜአ)፦አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸውን የሰበር ውሳኔዎች በኤሌክትሮኒክስ አማራጮች ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሕትመት ተዘጋጅተው ከቅጽ 19 እስከ 26 የወጡ የሰበር ውሳኔዎችን በድምጽ ቅጂ እንዲዘጋጁ በማድረግ ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር አስረክቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ከቅጽ 1 እስከ 18 በሕትመት የተዘጋጁ የሰበር ውሳኔዎችን በድምጽ ቅጂ አዘጋጅቶ ለብሔራዊ ማሕበሩ ተደራሽ ማድረጉ ይታወሳል፡፡


 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ ፍርድ ቤቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸው ውሳኔዎች በኤሌክትሮኒክስና ህትመት ሚዲያዎች በማሰራጨት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድምጽ ቅጂዎች ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል እንዲያገኛቸው በሕትመትና በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚሰራጩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቅጂዎቹን በኤሌክትሮኒክስ አማራጮች በስፋት ተደራሽ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ውሳኔዎቹን በዩቱዩብ ቻናል በመጫን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ማህበር ፕሬዝዳንትና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ረታ በበኩላቸው፥ ቅጾች የያዟቸው አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች ለአይነ ስውራን ተደራሽ መሆናቸው ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

በተለይም ለአይነ ስውራን መብትና ግዴታን በማጎናጸፍ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም