ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ የማጓጓዝ ስራ እየተፋጠነ ነው

አዳማ፤ሐምሌ 23/2017 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ በመርሐ ግብር ለምግብነት የሚውሉትን ጨምሮ የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚውሉ ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ የማጓጓዝ ስራ እየተፋጠነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ችግኝ የማጓጓዙ ተግባር እየተፋጠነ ነው።

በዞኑ 11 ወረዳዎች ውስጥ በተሽከርካሪና በሰው ኃይል በመታገዝ የችግኝ ማጓጓዙ ስራ በተቀናጀና በተሳለጠ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶ አደሮች የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዕለቱም ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎች፣ለውበት እና ለሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ ችግኞች በብዛት እንደሚተከሉ ገልጸዋል።

በሁሉም አካባቢዎች በተመረጡ የችግኝ መትከያ ስፍራዎች ላይ የዞኑን ህዝብ ያሳተፈ የጉድጓድ ዝግጅት ቀደም ብሎ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ አርሶና አርብቶ አደሩን ጨምሮ መላው የዞኑ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አውስተዋል።

ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተሰጠው ትኩረት የተጎዱ አካባቢዎችን ልምላሜ ከማላበስ ባለፈ ለሁሉም የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገትና የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አቶ አብነት አብራርተዋል።

የዞኑ ወጣቶች በበኩላቸው፥ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ከልጆች ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍሎች በተከላው እንዲሳተፍ ህዝቡን የማንቃት ስራ እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም