ቀጥታ፡

የአንድ ጀንበር አሻራ ከጅማሮው እስከ አሁን

የደን መጨፍጨፍ፣ የመሬት መራቆት እና የአየር ንብረት ለውጥ ከምድር ከባቢ አየር አልፎም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስጋቶችን ደቅኗል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በደን ልማት አማካኝነት ስነ ምህዳሮችን ዳግም ወደ ነበሩበት የመመለስ፣ ብዝሃ ህይወትን የመጠበቅ፣ የካርቦን ልቀትን የመቀነስ እና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከጀመረች ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል።

2011 ዓ.ም ክረምት መባቻ አረንጓዴ አሻራ የተጀመረበት ወቅት ነው። እስከ አሁን በመርሃ ግብሩ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

የዚህ መርሃ ግብር ልዩ ገጽታው ማህበረሰብ በአንድ ጊዜ በነቂስ ወጥቶ የሚተሳተፍበት መሆኑ ነው።

ይህም አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ ተከላ ባለፈ የአንድነት፣ የብሄራዊ ክብር እና የአይበገሬነት መገለጫ አድርጎታል።

በአረንጓዴ አሻራ በቋሚነት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ይገኝበታል።


 

የብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ግዛው በ2011 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ ሲጀመር በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 354 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድ ጀንበር መርሃ ግብር አለመከናወኑን አመልክተዋል።

ይሁንና በነዚህ ዓመታት ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የራሳቸውን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አዘጋጅተው እንዲተክሉ ተወስኖ ስራው መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዚህም በ2012፣ 2013 እና 2014 ዓ.ም ክልሎቹ በየዓመቱ በአጠቃላይ በአማካይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከላቸውን ጠቁመዋል።

አንድ ጀምበር በሀገር አቀፍ ደረጃ በድጋሚ በ2015 ዓ.ም መመለሱን አስታውሰው በዚሁ ዓመት 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከታሰበው በላይ 566 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ነው ምክትል ሰብሳቢው ያብራሩት።

በ2016 ዓ.ም 600 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከል እቅድ ተይዞ 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።


 

በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነገ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ነገ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን አካል የሆነውን በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል አላማን ለማሳካት እንነሳለን ሲሉ ገልጸዋል።

ከፍ ያለ ግብ ቢሆንም ያለን መሻት ጥንካሬያችንን፣ አንድነታችንን እና ለሕዝባችን ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ሰው በዚህ ታላቅ ሥራ እንዲሳተፍ እና እንዲያስተባብርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም