ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራት የከርሰ እና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጎለብት አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራት የከርሰ እና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጎለብት አስችለዋል
ሰመራ፤ ሐምሌ 23/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራት የከርሰ እና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጎለብት ማስቻላቸውን በአፋር ክልል የአረንጓዴ ዐሻራቸውን ያኖሩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞች በአፋር ክልል አሚበራ ወረዳ ኮማጊደሮ ቀበሌ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
በዚህ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር) እንዳሉት ላለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት የከርሰ እና ገፀ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጨምር አድርገዋል።
ችግኞቹ ዘርፈ ብዙ ጥቀሜታ ያላቸው መሆናቸው የውሃ ብክነትን ከመከላከል ባሻገር በጎርፍ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን ማስቀረታቸውን በጉብኝታችን ተመልክተናል ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) በኩላቸው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባሻገር የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን መታደግ እንደቻሉ ገልፀዋል።
በተለይም በአፋር ክልል የተሰሩት የአረንጓዴ ዐሻራ ስራዎች የውሃ አቅሞችን በመጨመራቸው የፍራፍሬና የመስኖ ልማቶች እንዲስፋፉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የአየር ጸባይ መዛባትን ለመቋቋም ተጨማሪ አቅም ፈጥረዋል ያሉት ደግም የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ናቸው።
ይህም በአየር ጸባይ ሚዛን መዛባት ይደርስ የነበረን የጎርፍና ሰደድ እሳት አደጋዎችን ለመከላከል የላቀ ጠቀሜታ ማበርከታቸውን አክለዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ ተከላውም ሆነ በመንከባከብ ህብረተሰቡ በነቂስ በመሳተፉ ለስራው ስኬት ማገዙን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታመነ ሐይሉ(ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን በመጨመር ለከረሰ እና ገጸ ምድር ውሃ መጎልበትና በረሃማነት በመከላከል የራሱ አበርክቶ ማድረጉን አስረድተዋል።
የችግኞች መተከል ለአካባቢ ጥበቃ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው ተግባሩን ማስቀጠልም ለመጪው ትውልድ ምቹ አካባቢን ለማውረስ መደላድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።