ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በቂ ዝግጅት ተደርጓል

ወላይታ ሶዶ ፤ሐምሌ 22/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በክልሉ ወላይታ ዞን ለመርሃግብሩ የተደረገውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 


 

በዚህ ወቅት እንደገለጹት በመጪው ሀሙስ በክልሉ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚካሄደው ለዚህ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በመርሀ ግብሩ ለችግኝ ተከላ በተመረጡ 973 ቦታዎችና ተፋሰሶች ላይ ከማለዳው ጀምሮ ተከላ እንደሚካሄድ ገልጸው በዚህም 9 ሺህ 421 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል።


 

በክልሉ በተመረጡ ሁሉም አካባቢዎች ለተከላ የሚሆኑ የጉድጓድ ቁፋሮ እና ችግኝ የማጓጓዝ ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም መሪሁን (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ክልላዊ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ ኮዶ ቃንቆ ቀበሌ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት እንደሚካሄድም መሪሁን (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

በእለቱ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም