ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ የብልጽግና ጉዞ ቀጣይነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ነው

ድሬደዋ፣ ሐምሌ 22/2017 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብልጽግና ጉዞ ቀጣይነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት መሆኑ ተመላከተ።

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ በድሬዳዋ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነፃ ንግድ ቀጠና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደዋል።በመርሃ ግብሩም የተለያዩ የጥላና የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በሐይሉ ንጉሴ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ አሻራ የአገራችንን የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቅ የብልጽግና ጉዞን እያሳካ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ በትውልድ ቅብብሎሽ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እያሳካ የሚገኝ ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለዜጎች በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሚያቀርበው የፍራፍሬ ምርቶች ፕሮጀክቱ መሠረታዊ መደላድልን እየፈጠረለት እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ነፃ የንግድ ቀጠና የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ አብያት ከበደ በበኩላቸው ዛሬ የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዞኑንና አካባቢውን ምቹ የስራ እና የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


 

ነፃ የንግድ ቀጠናው የሚፈለግበትን ተልዕኮ በትክክል ለማሳካት ብሎም  ወደ ቀጠናው ለሚገቡ ባለሃብቶች ምቹና ሳቢ የስራ ቦታ ለመፍጠር የቀጠናውን ሰላሳ በመቶ አረንጓዴ የማልበስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ ፀድቀው አካባቢውን እየለወጡ መሆኑንም በማከል።

ነፃ የንግድ ቀጣናው ያለበት አካባቢ ስራ በጀመረበት ወቅት ገላጣና አቧራማ እንደነበረ አስታውሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ግን መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን የገለፁት ደግሞ በችግኝ ተከላው የተሳተፉት ወይዘሮ ፎዚያ መሐመድ ናቸው።


 

ነፃ የንግድ ቀጠናው እሳቸውን እና በመቶዎች የሚገመቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን በማህበር በማደራጀት በአረንጓዴ ልማት ላይ የስራ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

"ዛሬ የተተከሉት ችግኞች በሙሉ ፀድቀው የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡም ክትትል እናደርጋለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም