በጥበብ ስራዎች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ይበልጥ የመገንባቱ ተግባር ይጠናከራል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
በጥበብ ስራዎች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ይበልጥ የመገንባቱ ተግባር ይጠናከራል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
ጎንደር፤ ሐምሌ 22/2017(ኢዜአ)፡- በጥበብ ስራዎች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ይበልጥ የመገንባቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ተናገሩ።
"ባሕል ጥበባትና ስፖርት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት "በሚል መሪ ሀሳብ የሚኒስቴሩ ጉባኤ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፤ በኪነጥበብና በስነጥበብ ዘርፍ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት የጋራ ገዢ ትርክቶችን ለማስረፅ በትኩረት ይሰራል።
የባህል እሴቶች ለሀገር ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቁመው፤ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠበቅ ለሠላም ግንባታው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማሳደግ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባሕልና ስፖርቱ ዘርፍ አመርቂ አፈጻጸም መመዝገቡን አውስተው፤ ሀገር አቀፍ የጥበብ ፖሊሲ ጥናት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የጥበብ ምክር ቤት ደንብ በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ባሕልና ቋንቋን ለማበልጸግና ለማሳደግ አስቻይ ሁኔታዎች የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአለም አደባባይ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ይበልጥ ለመገንባት የሚያስችሉ " የኢትዮጵያ ብስራት ማሳያ" በሚል የኪነጥበብ ቡድን በአለም ዙሪያ ዝግጅቱን እያቀረበ ይገኛል ሲሉም አንስተዋል።
ባሕልና ኪነጥበብ ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ ሂደት አይተኬ ሚና አላቸው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ መልካሙ ጸጋዬ ናቸው።
የባሕል እሴቶቻችን ለሠላም ግንባታና ለሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓታችን መጎልበት አስተዋጽኦቸው ከፍ ያለ ነው፤ ለሕዝብ ትስስርና አንድነት የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ፤ ጎንደር በሀገረ መንግስት ግንባታ የራስዋን የባህል የታሪክና የስነ ጥበብ አሻራዋን ያሳረፈች ከተማ ነች ሲሉ ገልጸዋል።
የባሕል እሴቶች ለህዝቦች የእርስ በርስ አብሮነትና መደጋገፍ ብሎም ገዢ ትርክትን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጎንደር ይህን ታሪካዊ መድረክ እንድታስተናግድ በመመረጥዋ በሕዝቡ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በጉባኤው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በ2017 እቅድ አፈጻጸም እንዲሁም በ2018 እቅድ አተገባበር ዙሪያ ግምገማና ውይይት እንደሚያካሂድ ለማወቅ ተችሏል።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የባሕልና ስፖርት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።