በክልሉ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል
ጋምቤላ፤ ሐምሌ 22/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የፊታችን ሐሙስ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በዕለቱ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬታማነት መላው የክልሉ ህዝብ በነቂስ በመውጣት አሻራውን እንዲያስቀምጥም ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል ለኢዜአ እንደገለጹት የፊታችን ሐምሌ 24 ቀን 2017ዓ.ም ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
በዕለቱ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ በክልሉ በተመረጡ 16 የተከላ ቦታዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በተከላ ቦታዎች አስፈላጊው የጉድጓድ ቁፋሮ፣ ችግኞች ወደ ተከላ ቦታ የማጓጓዝና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው እለቱ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ772 ሄክታር መሬት ላይ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 75 ከመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በዕለቱ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መላው የክልሉ ህዝብ ከጧቱ 12:00 ጀምሮ በተከላ ቦታዎች በመገኘት አሻራውን በማስቀመጥ የዜግነት ኃላፊቱን እንዲወጣ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
እንደ ሀገር ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ. ም በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙ የሚታወስ ነው።