ቀጥታ፡

ሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ። 

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር የሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል።


 

ሀገራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠበቅና ቆሻሻን መልሶ መጠቀም የሚያስችልና የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ሀገራዊ ፍኖተ ካርታው አራት ዓላማዎች ያሉት መሆኑን ተናግረዋል።

ፍኖተ ካርታ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ አካባቢን ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለአረንጓዴ ስራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል። 

ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በመስራት የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅና ፅዱ ኢትዮጵያን የመፍጠር ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህም ፈጠራን የሚያበረታታና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም በራስ አቅምና ግብዓት ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።  

የስራ እድል ፈጠራን የሚያበረታታና በአለም አቀፍና አፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ እንደሚያግዝም ገልፀዋል።


 

የአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካይ መንግስቱ በቀለ በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው ከኢትዮጵያ አገራዊ ግብና ባንኩ በአገሪቱ ቅድሚያ ከሚሰጠው ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል። 

ፍኖተ ካርታው ለአካባቢ ጥበቃና ለስራ እድል ፈጠራ ሚና እንዳለው ተናግረው ለፍኖተ ካርታው እውን መሆን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ እንደነበር አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ(ዶ/ር) በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታው ተረፈ ምርትን በምርት ግብዓትነት ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ኢንስቲትዩቱ ከደረጃ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በመስራት ለፍኖተ ካርታው ውጤታማነት የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግረዋል።


 

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ(ዶ/ር) ፍኖተ ካርታው ለተረፈ ምርቶች አስተዳደር ሚና ያለው መሆኑንና ኢንስቲትዩቱም በዚህ ረገድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም