ቀጥታ፡

ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የተጣጣመ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የተጣጣመ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አፍሪካ ግብርናን በማዘመንና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቋቋም የምግብ ስርዓትን ማሳለጥ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦት ያስፈልጋታልም ብለዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ከጣልያን እና ከተመድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው 2ኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል፡፡

ኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማረጋገጥ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በትምህርት ቤት ምገባ ያስመዘገበቻቸው አስደናቂ ውጤቶችን በተሞክሮነት የምታቀርብበት ጉባኤ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ከውጭ የሚገባውን ምርት በመቀነስ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው፡፡

ይሄውም በኢትዮጵያ የማይበገር የምግብ ስርዓት በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ ይፋ ማድረጓን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፍኖተ ካርታው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የተጣጣመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይሄውም በግብርናና መሬት አስተዳደር ስርዓት ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት አካታች የማይበገር እና ዘላቂ ማድረግን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን ለማዳረስ ከ700 በላይ የሆኑ የድርጊት መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

ሁሉንም ያሳተፈ ሽግግር በማድረግ ውጤቶችን በተግባር ማየት ጀምረናል ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት፣ የሰቆጣ ቃል ኪዳን የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዬን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃንና የአየር ንበረት ለውጥን ለመከላከል ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ቤት ምገባ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎችን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በግብርና፣ በገጠር መሰረተ ልማት እና የተመጣጠነ ምግብ ልማት ላይ የኮንሴንሽናል ፋይናንስ/ አነስተኛ ወለድ ያለው የብድር ፋይናንስ እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል፡፡

ረሀብና የአየር ንብረት ለውጥ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የአየር ንብረት ፋይናንስ ከምግብ ሥርዓት ጋር መያያዝ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ላይ ዝቅተኛ አስተዋጽኦ ቢኖራትም የበለጠ ተጠቂ መሆኗን በመግለጽ፤ የአየር ንብረት ፋይናንስ ከልማት ጋር መተሳሰር አለበት ብለዋል፡፡

አፍሪካ ስማርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እውን ለማድረግ ሁሉንም በተመጣጣኝ ሁኔታ ማግኘት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

የመሬት አጠቃቀምና ዘላቂ የግብርና ልማት የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳለጥ እርዳታ ሳይሆን የጋራ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ተግባር መግባት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ከፋይናንስና ቴክኖሎጂ ባሻገር በዓለም የንግድ ውድድር ስርዓት ፍትሐዊ ተጠቃሚ የምትሆንበት አሰራር መኖር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎችም አጋሮች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም