የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ስኬት ለአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ስኬት ለአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ስኬት ለአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሁለተኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የጉባኤው ተሳታፊዎች የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከልን የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
የምርምር ማዕከሉ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ሥር ካሉ 22 ማዕከላት ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የእህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው።
ማዕከሉ ለምግብ ዋስትና እውን መሆን ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ሲሆን፤ ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍ ያሉ የእህል ዝርያዎችን በማውጣት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።
ባለፉት ዓመታትም የምርምር ማዕከሉ ከ1600 በላይ ዝርያዎች በምርምር ማውጣቱም ተጠቅሷል።
ከጎብኚዎቹ መካከል የቦስትዋና የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ ወጣት ባንግ ኔልሰን ንቲሜ እንዳለው፤ በኢትዮጵያ በግብርና መስክ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው።
የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር በመታገዝ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የጀመራቸው ውጤታማ ሥራዎች ለዚህ ማሳያ መሆኑንም ገልጿል።
በማዕከሉ በነበረኝ የጉብኝት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ብዛት ያላቸው የምርምር ውጤቶች አይቻለሁ ሲሉም ጠቅሷል።
በማዕከሉ ያሉ ተሞክሮዎች በርካታ የአፍሪካ አገራት በአርአያነት ሊወስዱት የሚገባ ውጤቶች ነው ብሏል።
የቦትስዋና ብሄራዊ የምርምር ኢኒስቲትዩት ከመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ብዙ መማር የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ተናግሯል።
በጉባኤው ላይ ለመታደም ከኡጋንዳ የመጣችው ወጣት ክርስቲና ናሙቢሩ በበኩሏ፤ የአፍሪካ አገራት ምርትና ምርታማንት የሚያሳድጉ ምርምሮች ጠንካራ ኢንቨስትመንት ሊኖራቸው ይገባል ብላለች።
ለምግብ የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት አቅም እንዲጎለብት የአፍሪካ አገራት እንደ መልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል ዓይነት ውጤታማ ተቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግራለች።